Friday, August 10, 2007

ስለ ኦጋዴን ጋዝ ከበሮ በዛሳ !!!

"የቬኑዜላ ፕሬዚዳንት ፣ ሁጎ ቻቬስ ፣ ከኢኳዶር አቻቸው ጋር 5 ቢሊዮን ዶላር ሊፈጅ ይችላል የተባለለት የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ ስምምነት አደረጉ" በተባለበት በዚህ ሰሞን የኢትዮጵያ መንግሥት በኦጋዴን ክልል በካሉብና ሃላል ያለውን ጋዝ ለማልማትና ወደ ዓለምአቀፍ ገበያ ለማቅረብ የማሌዥያ መንግሥት ንብረት ከሆነው ፔትሮናስ ጋር የ1.9 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ኩአላ ላምፑር ላይ መፈራረሙ እኔን አላስደነቀኝም ። ዕድሜ ልካችንን ስንታለልበት ለከረምነው የኢትዮጵያ የነዳጅ ጉዳይ አሁንም ፣ አሁንም እየደጋገማችው ግራ አታጋቡን ። አንዲት የነዳጅ ጠብታ በዓይናችን ሳናይ በራዲዮና በቴሌቪዥን ብቻ አታደንቁሩን ። ከአሥር ዓመት በፊት ይኸው የኦጋዴን ነድጅ ሊወጣ ነውና "አክሲዮን ግቡ "ብላችው ነበር ። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ወሬው እሱ ብቻ ነበር ።የአክሲዮኑ ነገር ደብዛው ጠፋ ። የሚያነሳውም የለም ። "ኡፈይ ! "ምርጫችን ባይሆንም "ኡፈይ ! "አልን ። ስለዚሁ የነዳጃችን ጉዳይ አንድ ጓደኛዬ "ነዳጁ ያለው ቴሌቪዥኑ ውስጥ ነው " ብሎ ከነገረኝ ቆይቷል ። አምኜዋለው ። ስለእውነት ፣ የአንዲት ሰሞን የፖለቲካ ኡኡታ ካልሆነ በቀር የ1.9 ሚሊዮን ዶላር ጋዝ የማውጣትና መስመር የመዘርጋት ስምምነት ይህን ያህል ምን ሆነና ነው ከበሮ የበዛለት? የጋዙ ማስተላለፊያ ቱቦ ወይም መስመር እውነት ኦጋደንን አቋርጦ ፣ ሞቋዲሾ ወይም ሶማሊላንድ በርበራ አልያም ጅቡቲ ወደብ ድረስ ይዘረጋል ? እሺ ፣ ስንት ጊዜ ስንት ዶላር ያስፈልገዋል ? የ1.9 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ለዚያ ሁሉ በቂ ነው ማለት ነው ? ወይስ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ደረቅ ቀልድ መቀለድ ስለማያሳፍራችው ያንኑ እንጨት እንጨት የሚል የገዳይ ቀልድ እንደለመዳችውት በኛ ላይ መልቀቃችው ነው ? ? ?

ወንድሞቼ ሆይ ፤ በየትኛው ሰላም በየትኛው ምቹ የልማት ወቅት ነው ይንን ለማድረግ ቆርጣችው የተነሳችውት ? ለሃገር አሳቢና ለሃገር ልማትና ዕድገት ተቆርቋሪ ብትሆኑ ኖሮ መጀመሪያ ጋዙ ካለበት የኢትዮጵያ መሬት ላይ እንደማንኛውም ዜጋ ኢትዮጵያዊ ሆነው ከሚኖሩት የኦጋዴን ሰዎቻችን ጋር መነጋገር ነበረባችው ። የኦጋዴን ህዝብ ደግሞ ከወያኔ ይልቅ የሚያደምጠው ኦብነግን መሆኑን እኛ አናውቅ እንደሆን እንጂ እናንተ አሳምራችው ነው የምታውቁት ፤ በአጩሜው ተዠልጣችዋልና !! ደሳሳ ጎጆውን በላውንቸር ከምታጋዩበት ፣ ዕርዳታ የሚያገኝበትን መንገድ ከምትዘጉበት ፣ ሴቶቻቸውን አስገድዳችው ከምትደፍሩባቸው ፣ የልማትና የሰብአዊ ሰራተኞቻቸውን ከምትገድሉባቸው ፣ ቀይ መስቀልን ከምታስወጡባቸው ይልቅ ከኦብነግ ጋር ገለልተኛ የሆኑ አስታራቂዎች ባሉበት በሶስተኛ ሃገር ላይ ብትመካከሩ ኖሮ እናንተ ከመረጣችሁት ፍጅት የተሻለ ነገር ባየን ነበር ። ግን አልሆነም ። ምክንያቱም እናንተ አንዴ በመግደል ተወልዳችዋል ። በመግደል አድጋችዋል ። በመግደል ሸምግላችዋል ። በመግደል አፍሮ የነበራችው መንደርተኞች ዛሬ በመግደል መላጣና ሸበቶ ሆናችዋል ። ብሩህ ዓይን የነበራችው ሰዎች ዛሬ በመግደል መነጽር ለብሳችዋል ። የናንተ ግድያ መቆሚያው የትና መች እንደሆነ ማንም አያውቅም ። 17 ዓመት ጫካ ገደላችው ። 16 አመት ከተማ እየገደላችው ነው ። ጋምቤላ ትሄዳላችው - ትገድላላችው ። ኦሮሚያ ትሄዳላችው - ትገድላላችው ። አዋሳ ትሄዳላችው - ትገድላላችው ። ጎንደር ትሄዳላችው - ትገድላላችው ። ኦጋዴን ትሄዳላችው - ትገድላላችው ። ከማን ጋር ነው መኖር የምትፈልጉት ? በኢትዮጵያ ምድር ከሚገኙት አብዛኛው ብሄረሰቦች ጋር ተናክሳችው ፣ ተቧጭቃችው ፣ ሆድና ጀርባ እሳትና ጭድ ሆናችው እንዴት ነው በሥልጣን መቆየት የምትፈልጉት ? ለመሆኑ እናንተ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ዓይነት ሥርዓት ለማስፈን ነው የበሽታና የረሃቡን ዱካ እየተከተላችው ከበሽታና ከረሃብ የተረፈውን ሰላማዊ ሰው ከዳር እስከ ዳር የምትፈጁት ? ? ? እና ደግሞ ከሁለት ወይም ከሶስት አልያም ከስድስት ወራት በኋላ ማነው በናንተ ጥይት የሚረፈረፈው ባለተራ ብሄረሰብ ? እሱን እያሰብኩ ነው የምጽፈው ። የግድያ ልክፍታችው ከገዛ ሃገራችን ድንበር ተሻግሮ የሰው ሃገር ድረስ መዝለቁ የታወቀ ነውና የናንተ መድፍ የሚረጭበት የሚቀጥለው ባለተራ ሃገርስ ማን ይሆን ? ? ?

ባለመድፍ ወንድሞቼ ፤ ከላይ ለጠየኳችው ጥያቄዎች ከቻላችው መልሱን ስጡኝ እንጂ የኦጋዴንን ህዝብ መግደላችውን በመገናኛ ብዙሃን ባስነገራችው ማግሥት ስለጋዝ አታውሩልን ። በ1.9 ሚሊዮን ዶላር የግለሰብ ሃብት የሆነ አነስተኛ አጂፕ የነዳጅ ማደያ እንጂ በሃገር ደረጃ የሃገር ሁሉ ከበሮ የሚደለቅለት የጋዝ ልማት ሰምቼም አላውቅም ። አንድ ቀን ለማደር ብላችው የማይሆን ዝባ ዝንኬ በመገናኛ ብዙሃን እየለቀቃችው ሚዲያውን አታርክሱት ። የአየር ጊዜውን አትጫወቱበት ። የቬኑዜላ ህዝብ ስለ 5ቢሊዮን ዶላር የነዳጅ ማጣሪያ ያወራል ፤እናንተ ገዳዮች ፈርዶባችው ስለ 1.9 ሚሊዮን ዶላር ጋዝ ወሬ ትለፈልፋላችው ። ማፈሪያዎች !!!

No comments: