Wednesday, July 18, 2007

ወያኔዎች ፤ መግደልና ማሰር አይሰለቻችሁም ወይ?
አሥራ ስድስት አመት ሙሉ ገደላችው ። አስራችው ። አሰደዳችው ። የቻላችሁትን ያህል ገንዘብ ዘረፋችው ። ጫካ ውስጥ የረባ ምሽግ እንኳ ያልነበራችው ፍጡሮች ዛሬ ቤተመንግስት የመሳሰለ መኖሪያ ቀልሳችው ትኖሩበታላችው ፤ የተረፋችሁንም ለፈረንጅ ታከራያላችው ። በኢትዮጵያ ምድር ሁሉም ነገር የናንተ ሆኗል ። የናንተ እጅና እግር የሌለበት ወይም ያልደረሰበት የንግድም ሆነ የልማት ተቋም የለም ። የኢትዮጵያን የልጅ ልጆች ሁሉ በዱቤ ቸብችባችው ዶላሩን ወስዳችሁታል ። በውጭ ያሉ ባንኮች ለዚህ ምስክር የሚሆኑበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ። ከአሁን በኋላ የሚወለዱ ኢትዮጵያዊ ህፃናት ከናታቸው ማህጸን ሲወጡ በአንገታቸው የዱቤ ሠርተፊኬት አንጠልጥለው መሆኑን ካወቅን ቆይተናል ። ወባን "አይዞህ በርታ" ብላችው አዲስ አበባ የጨመራችው ጥቂት ማፍያ ሠዎች ይህ ሁሉ የናንተ ሆኖ ሰላማዊውን ዜጋ ትገድላላችው ፤ ታስራላችው ፤ ታሰቃያላችው ። ምን አድርግ ፣ ምን ሁን ነው የምትሉት ? እሽ ምን እንሁን ? ....... ንገሩን እንጂ !!!



እንዴት አንድ "ጭቆና አንገፈገፈኝ!" ብሎ ጫካ ውስጥ መከራውን የበላ ፤ የተናቀና የተዋረደ ቡድን በለስ ቀንቶት መንግሥት የመሆን እድል ሲገጥመው ተመልሶ ጨቋኝ ይሆናል ? ያውም የከፋ ! ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀው ጨቋኝና ውሸታም መንግሥት !! .....ለጋዜጠኛ የእድሜ ልክ ፍርድ የሚሰጥ መንግሥት !! ..... ሰላማዊ እንደሚሆን በተነገራቸው የምርጫ ሂደት ላይ የተሳተፉ ምሁርና ሽማግሌ ባለራእይ ዜጎችን የእድሜ ልክ እስር የሚሸልም እርጉምና በራሱ የማይተማመን መንግሥት - ያውም አሸንፈውት ። ለምረጡኝ ዘመቻ የተጠቀሙበትን የቅስቀሳ ንግግር ለመክሰስ የተጠቀመ ፤ ከዚያም የእድሜ ልክ እስራት የበየነ ዓይን አውጣ መንግሥት !! ጠመንጃችው ከጀርባቸው ዞር ቢል ባዶ ሆናችው የምቀሩ እናንተ የገዳይ ማህበር አባላት እባካችው ህዝቡን እስቲ ምን አድርግ ፣ ምን ሁን ነው የምትሉት ? እሽ ምን እንሁን ? ...... ንገሩን እንጂ !!!



በምርጫው ሰበብ ያሰራችኋቸውን አሸናፊ ተመራጮች አንገታችሁን ተይዛችው መፍታታችው ላይቀር ለምንድ ነው ሁለት አመት ሙሉ ያሰቃያችዋቸው ? የህግ ሥርዓታችሁ የበሰበሰና የገማ መሆኑን ማንም ነው የሚያውቀው ። በሱ መነገድ እንደሆን አይቻልም ። ይሄ የሰለጠኑና ሰርቲፋይድ የሆኑ ምስክሮችን ከየትም እየለቃቀመ "በምስክር ስም" ለችሎት የሚያሰማ ፍርድ ቤት የናንተ አንዱ የማጥቂያ ብርጌድ ነው እንጂ ፍርድ ቤት አይደለም ። ለምን "መብረቅ" ወይም "በርቂ" ወይም " ክብሪት ብርጌድ" ወይም "ሬጅሜንት" አትሉትም !! እንደዚያ ብትሉት ነበር የዓለም ህብረተሰብ የሚያምናችው ። ለዚያው ሰርቲፋይድ ምስክሮቹ ሰርቲፋይድ ያልሆኑበትን የእውነት ቃል ሲለፈልፉ እየተሰማ ። እነዚህን ሰዎች ለመፍታት ሺ ስም ብትሰጡ "ምህረት" ፣ "ይቅርታ ጠየቁ" ፣ "ስህተታቸውን አመኑ " ፣ ግማሽ ሃላፊነት ወሰዱ" ብትሉ ፤ የፈለጋችሁትን ቃላት ብትደረድሩ አምኖ የሚያዳምጣችው የለም ። ሰዎቹ የሚፈቱት አንገታችሁን ስለተያዛችሁ ብቻ መሆኑን ነው የምናውቀው ። የታሰሩትም ስላሸነፏችው ነው - ያውም በዝረራ ! በባዶ ! በዜሮ ! ታንክ ሳይኖራቸው...... ይህን እወቁ ። ማንም አይረሳም ። ከማንም ኢትዮጵያዊ ህሊና ውስጥ የሚፋቅ ታሪክ አይደለም ። የሚፈቱትም ስላሸነፏችሁ ነው - ታንክ ሳይተኩሱ ። እነሱን እስር ቤትአጉራችው እናንተም እኛም እንቅልፍ የለንም ። ኢትዮጵያዊው በሙሉ አይተኛም ። አልተኛም ። ይህን ታውቃላችው ። ከምርጫው በፊት የነበረው አተኛኘታችውና አተኛኘታችን ከምርጫው በኋላ ተለዋውጧል ። ግን ግን እኔ የማይገባኝ መግደል የምታቆሙት መች ነው ? ማሰርስ ? እንደናንተ ማሰርና መግደል የሚወድ የለምና !!



አንድ ነገር ልንገራችው ። አዲስ ነገር አይደለም የምነግራችው ። 16 አመት ሙሉ የኢትዮጵያ ህዝብ የነገራችውን ነው የምነግራችው ። መንገር ሳይሆን ማስታወስ ልበለው መሰል ። ሰላማዊ ሰዉን በየአስፋልትና ገጠር ላይ ስለደፋችሁት ፤ ጨለማ ቤት ስላጎራችሁት ፤ እንደለመዳችሁት 40 ሺ ወጣት ሰብስባችው ስለቀጠቀጣችው ወይም ስላሰራችው ፤ እድሜ ልክ ወይም 20ና 30 አመት ስለፈረዳችው ፤ የኢትዮጵያዊው የለውጥ ስሜት ፣ ጉጉት ፣ የመናገር ፣ የመሰብሰብ ፣ በፈለገው የሙያም ይሁን የፖለቲካ ማህበር የመደራጀት ፣ በመረጠው የፖለቲካ ሥርዓት ጎዳና መጓዝና ከልቡ በመረጠው ተመራጭ መተዳደር ተስፋው አይሞትም ። ምንም ተባለ ምን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ይኸው ይፍፈጸማል ። የሠው ልጅ የለውጥ ስሜት በመግደል አንድ ቦታ አይቆምም ። ለውጥን በማሠር ማገድ አይቻልም ። ለውጥ ሂደት ነው ። ይሄዳል ። የኢትኦጵ መጽሄትና ጋዜጣ አሳታሚ ድርጅት ባለቤት የሆነውን ጋዜጠኛና አሳታሚ ሲሳይ አጌናን ወደ 100 ሺ የሚገመት ጥሬ ገንዘብ "ለምርመራ" በሚል ሰበብ ቀምቶ ዛሬ ደግሞ 100ሺ ብር እንዲከፍል ፍርድ ቤቱ መፍረዱ ምንድ ነው የሚባለው ? ። የፈለገ ዓይነት የጭካኔ ፍርድ ከፍርድ ቤቶቹ ብርጌድ ቢተኮስ ለውጥ ኢትዮጵያ ውስጥ አይቀርም ። እናንተ ምን እንደምትሉን ባይገባኝም እኔ በበኩሌ እንዲገባችሁ አድርጌ የምለው አለኝ - " እያንዳንችሁ የእጃችሁን ታፍሳላችው ..... በንጹሃን ደም የበሰበሰው እጃችሁና በዘረፋና በትዕቢት ያበጠው ልባችው አንድ ቀን ፍርዱን ከኢትዮጵያ ህዝብ ያገኛል ። በመንግሥትነት ስም በቡድን ተደራጅተው የኢትዮጵያን ህዝብ የገደሉ ሁሉ ሲዋረዱ አይተናል ። እናንተም ከዚያ ውርደት አታመልጡም ።

በመጨረሻም ..... ምን አድርግ ፣ ምን ሁን ነው የምትሉት ? እሽ ምን እንሁን ? ..... ንገሩን እንጂ ! መደብደብ ፣ ማሰር ፣ መግደል ፣ በቶርቸር ማሰቃየት ፣ ማሰደድ ፣ ባንክ ዘራፊ ሆናችው "ባንክ ዘራፊ ነው .... የሰለጠነ አድማ በታኝ ፖሊስ እና ውኋ መርጪያ የለንም" ማለት አይሰለቻችሁም ። ስንት መሬት ፣ ስንት ሰላማዊ ሰውና ስንት ብር ነው መብላት የምትፈልጉት ? ? ? ? ? ጅቦች !! የሠው ጅቦች !!!!






No comments: