የኢትኦጵ መጽሔት ርዕሰ አንቀፅ
"ድል እያሸተተ ያለ ህዝብ ውጤቱ እንዲቀለበስ አይፈቅድም"
( ቅፅ 6 ቁጥር 70 ግንቦት 97 ዓ.ም )
ዛሬ በእስር ላይ የሚገኙት የኢትኦጵ አሳታሚና ጋዜጠኞች ለገዳዩ የወያኔ መንግሥት ከዚህ በታች የተመለከተውን መልዕክት አስተላልፈው ነበር ። ከበረሃ አውሬነት ወደ ቤተመንግሥት አውሬነት የተለወጠው የወያኔ መንግሥት ግን አልሰማቸውም ። እንዲያውም አውሬነቱን በላይ በላይ ጨመረበት እንጂ !!
"ሐሙስ ግንቦት 18 ቀን 1997 ዓ.ም በዩኤስ አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያደረጉት እጅግ ደማቅ ትዕይንተ ሕዝብ እስከዛሬ በአሜሪካ ኢትዮጵያውያን ካደረጉት ሰልፍ የላቀ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የተገኘበት መሆኑ ተረጋግጧል ። ኢትዮጵያውያን በፍፁም የወንድማማችነት ስሜት በአንድነት ቆመው በአንድ ድምፅ ለሐገራቸው ትንሳኤ ጮኸዋል ። ልዕለ ኃያል የሆነችው ዩኤስ አሜሪካ በኢትዮጵያ የተካሄደውን ምርጫ ለማዛባት የሚደረገውን ጥረትና ሂደቱን በጉልበት ለመቀልበስ የሚደረገው ጥረት እንድትከታተልና የህዝብ ድምፅ እንዳይሰረቅ ግፊት ታደርግ ዘንድ ተማፅነዋል ። የህብረቱም ይሁን የቅንጅቱ ደጋፊዎች በአንድነት በአንድነት ቆመው ድምፃቸውን ያስተባበሩበት ይህ ትዕይንት የአሜሪካውያንንም ሆነ የሌሎች ሃገሮችን ትኩረት የሳበ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።
በመቶዎች ፣ አንዳንዴም ከዚያ በታች ፣ ግፋ ቢልም ከአንድ ሺህም የማይልቁ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች በዋሽንግቶን ጎዳናዎች ላይ ሰልፍ ሲያደርጉ የታዩ ቢሆንም ፣ ከአሥር ሺህ ሕዝብ የሚልቅ ኢትዮጵያዊ በአንድነት አደባባይ ሲወጣ ይህ የመጀመሪያ ነው ። በአሜሪካ የሚኖሩየውጭ ሐገር ዜጎች በሐገራቸው ጉዳይ ላይ ተሰባስበው በእንዲህ ያለ መጠን ትዕይንተ ሕዝብ ሲያካሂዱ የኢትዮጵያውያን የመጀመሪያው መሆኑም ተነግሮለታል ። በአሜሪካ ርዕሰ መዲና ዋሽንግተን ላይ የተስተጋባው የኢትዮጵያውያን የአንድነት ድምፅ በጀርመን በርሊን ላይም ተስተጋብቷል ። በሌሎች የአውሮፓ ከተሞችና ከአውሮፓ ውጭ ባሉ ሐገራት ከተሞችም ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል ።
ኢትዮጵያውያን በሐገር ውስጥም ሆነ ከሐገር ውጭ በከፍተኛ መጠን በአንድነት ቆመው የጋራ ድምፃቸውን ሲያስተባብሩ የቆዩ ቢሆንም ሚያዝያ 30 በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የታየው ትዕይንት ፣ በክፍለ ሃገር ከተሞችም ተቃዋሚዎችን ለመደገፍ የወጣው ሕዝብ ብዛት ፣ እንዲሁም በዩኤስ አሜሪካ ዋሽንግተን ላይ የታየው ሰልፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ የላቀ ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የለውጥ ተስፋን የሰነቀ ሆኖ ቀጥሏል ። ይህ ትብብር ፣ መነሳሳትናበሕዝቡ ውስጥ በከፍተኝ ደረጃ የሰረፀው የለውጥ ስሜት ከእንግዲህ የጠመንጃ አገዛዝ በዚች ሐገር እንዲያበቃ የማድረግ ኃይል እንዳለውም ሊሰመርበት ይገባል ። በከፍተኛ ስሜት የተነሳሳንና ድሉን ማሽተት የጀመረ ሕዝብ ድምፁ ሲቀለበስ ፣ የጉልበት አገዛዝ ሲነግስ ከቶውንም በዝምታ አይመለከትም ። እንደተለመደው ነገሮችን በማምታታትና በማስፈራራት በመጣንበት መንገድ እንቀጥላለን የሚሉ ካሉ አቋማቸውን እንደገና ቢመረምሩ ከማንም በላይ ተጠቃሚዎች እነርሱ ይሆናሉ ።
ዛሬ ሥልጣን ላይ ያለው የአቶ መለስ መንግሥት የዛሬ 14 ዓመት ሥልጣን ላይ ሲወጣ የሶሻሊስቱ ጎራ ፈርሶ ፣ የካፒታሊዝም ርዕዮተዓለም ነግሶ ፣ ዓለም በተለይም ታዳጊ ሐገራት የልዕለ ኃያሏ ዩኤስ አሜሪካ ተከታይ ከመሆን ውጭ አማራጭ ያልነበረበት ሁኔታ ነበር ። በመሆኑም በትግል ላይ በነበረበት ወቅት እንደ ደርግ ሁሉ ሶሻሊዝምን ሲያቀነቅን የነበረውና እንዲያውም የአልባኒያ ሶሻሊዝም አድናቂና ተከታይ ሆኖ የዘለቀው የሕወሓት/ኢሕአዴግ ቡድን ወደ ስልጣን ሲመጣ ባሉት አስገዳጅ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትንና ሃሳብን የመግለጽ ነፃነትን በመቀበል በዚህች ሐገር የዴሞክራሲ መስረት እንዲጣል ማድረጉ በምንም የማይስተባበል ቢሆንም ፣ በሐገራችን ከነበሩት መንግሥታት ሁሉ ፍፁም በተለየ ሁኔታ በኢትዮጵያውያን ላይ ጥርጣሬንና ጥላቻን በማንገስ ፣ በኢትዮጵያውያን ኪሳራ ባዕዳንን ለማበልፀግ የተንቀሳቀሰ ፣ ዘረኝነትን ያነገሰ የጥላቻ ቡድን መሆኑን ፀሃይ በወጉ ያገኘው ሃቅ ነው ። ስለ ኢትዮጵያዊነት መናገር የተወገዘበት ፣ ስለ ባንዲራ ክቡርነት ማዜም እንደወንጀል የተቆጠረበት ፣ ሰዎች በእውቀታቸው ሳይሆን በዘራቸው ወደ ሥልጣን የተሰባሰቡበት ፣ በዘር ልዩነት ዕልቂት የነገሰበት ፣ ንፁሃን የተፈጁበትና የተጨፈጨፉበት አስቀያሚና አሳፋሪ ሁኔታን በኢትዮጵያ ያነገሰው ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው የአቶ መለስ ቡድን ነው ።
አቶ መለስ ስለ ኢትዮጵያውያን አንድነት የሚነገረውን ለማጣጣልና ልዩነትን ለማስፋት " የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ምኑ ነው ?" ከማለታቸውም ባሻገር ታሪካዊውንና የነፃነት ተምሳሌት ሆኖ የዘለቀው ሰንደቅ አላማችን " ጨርቅ " ነው በማለት ማራከሳቸው የማይረሳ ነው ። ከግንቦት 1997 ምርጫ ዋዜማና ከምርጫው ወዲህ ስለ አክሱም ሃውልት የተናገሩትንና ስለ ባንዲራ የሰጡትን አስተያየት ማስተባበል ጀምረዋል ። ማስተባበያቸው ግን ፍፁም እውነትነት የለውም ። ዛሬ ከ 14 ዓመት በኃላ ጉዳዩን አንስቶ ምክንያት መደርደር ዋነኛ ግቡ በስልጣን ለመቀጠል ለኢትዮጵያውያን የተሰጠ የአፍ ጉቦ እንደሆነ ይታመናል ። አንዳንዶች እንደሚሉት ጠ/ሚ/ር መለስ ተፀፅተውም ከሆነ ከእሳቸው የሚጠበቀው የዕብሪት ንግግሮችን በውሸት መቀባባት ሳይሆን ፣ በይፋ ይቅርታ መጠየቅ ነው ። ከይቅርታም በላይ የሚሆነውና አቶ መለስ ዜናዊን ለዘለዓለም በመልካምነት የሚያስታውሳቸው ፣ የእስከዛሬውን ግፍና ጉድፍ ነቃቅሎ የሚጥልላቸው ግንቦት 7/1997 በሐገራችን የተከሄደውን የምርጫ ውጤት ያለአንዳች ማጭበርበር በፀጋ ሲቀበሉ ብቻ ነው ።
ታዛቢዎች ባሉባቸው አዲስ አበባን በመሳሰሉ ዋና ዋና ከተሞች በዜሮ የተሸኘው የአቶ መለስ ቡድን በገጠር በከፍተኛ ድምፅ አሸንፊያለው ሲል የሰጠው መግለጫ ጥርጣሬን የሚጋብዝ ከመሆኑም ባሻገር ፣ በተግባር ሲታይ በማጭበርበር የተሞላ ስለመሆኑም ማስረጃ ቀርቧል ። በመሆኑም የአቶ መለስ ቡድን ለሕዝብ ድምፅ በመገዛት በዚህች ሐገር ታሪክ መስራት ይጠበቅበታል ። ከእንግዲህ በጉልበት ለመቀጠል መሞከር የማያዋጣ እና ውርደትን የሚጋብዝ ከመሆኑም ባሻገር የስርዓቱን ወንጀልም የከፋ ያደርገዋል ። በጠመንጃ እንሞክረውና ካልሆነ እንሸሻለን የሚል ከልክ ያለፈ የስልጣን ጥም መድረሻው ከርቸሌ ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ አይከፋም ።
ከስልጣን መውረድ የዓለም ፍፃሜ አይደለም ። በሰላማዊ መንገድ ስልጣን መልቀቅ እንደገና በሕዝብ ድምፅ ወደ ስልጣን ለመውጣት እና በፍቅር ለመኖር ዋስትና ነው ፤ አቶ መለስ ለሕዝብ ድምፅ ራሳቸውን አስገዝተው ለቀጣዩ ምርጫ ይዘጋጁ ። እርግጥ ነው ይህ በዘር የተቧደነና በጥቅም የተሳሳበ የእንብላው ማህበር ጥቅምና ስልጣን ከሌለ የሚበተን መሆኑ ቢታመንም ፣ ፍላጎቱ ካለ ጥቂት የተሻሉ ሰዎች ከብዙ ግብስብሶች የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆኑ የሚያጠራጥር አይሆንም ። ከዚህ ውጪ ይህቺን ሐገር በመበተን ለኤርትራ ነፃነትም ሆነ ለአሰብ ወደብ ዋስትና እናስገኛለን የሚለው ድብቅ አጀንዳ ተደርሶበታልና ከእንግዲህ አይሰራም ። "
Thursday, November 09, 2006
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment